Notice አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሄደ።

አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሄደ።

19th February, 2024

ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሄደ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ "በትምህርት ሥርዓታችን ምን ዓይነት ትውልድ እንገንባ" በሚል ርዕስ ከትምህርት አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ መነሻም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ተለዋዋጭና ውስብስብ በሆነው የአለም ሁኔታ የነገን ትውልድ የመፍጠር ኅላፊነት ተሰቶናል። በመሆኑም አሁን ያለን የትምህርት ማህበረሰብ አባላት የምናስተምራቸው ተማሪዎች ምን ዓይነት እውቀት ይዘው ቢወጡ ይህንን መቋቋም ይችላሉ የሚለውን አስቦ መስራት ይገባል ብለዋል።
አክለውም የትምህርት ስርዓቱን ከፖለቲካ ወጣ ብሎ ወደፊት ምን መሆን እንዳለበት ማሰብ ያስፈለጋል ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ በተለይም ልዩ ችሎታና ተሰጥዖ ያላቸውን ተማሪዎች ባማከለ መልኩ በትምህርት ዘርፉ የምንሰራው ስራ ወደፊት ምን ለማግኘት ነው የሚለውን መመለስ መቻል አለበትም ብለዋል።
በዚህም ከሌላው አለም ጋር መወዳደር የሚችሉ፣ ችሎታ፣ እውቀት፣ ክህሎት፣ ግብረ ገብነትና ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች እንዴት መፍጠር እንችላለን የሚለውን መመለስና ለዚህም መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በትምህርት ላይ በሚሠራው ስራ መግባባትና በምክኒያት የሚያምኑ ዜጎችን መፍጠር ቢቻል ኖሮ አሁን በሀገራችን የሚስተዋሉ ችግሮች አይፈጠሩም ነበር ያሉ ሲሆን በዚህም የትምህርት ማህበረስቡና አመራሩ የትምህርት ስርዓቱን በመለወጥ ረገድ መግባባት ላይ መድረስ መቻል አለበት ብለዋል።
ተማሪዎችን እንደየ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው ማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት መኖር እንዳለበት ያነሱት ተሳታፊዎች በተለይም ለሳይንስ፣ ለምህንድስና፣ ለቴክኖሎጂና ለሂሳብ ትምህርቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ዓለም አቀፍ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይገባልም ብለዋል።
በተለይም በጥልቀት የሚያስብ፣ ሀገሩን የሚወድና ማሳደግ የሚችል ትውልድ በትምህርት ስርዓቱ እየተፈጠረ መሄድ እንዳለበትም በመድረኩ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የፈተና ስርዓቱ ተማሪው ምን ያህል እውቀት አለው የሚለውን የሚለካና የሚሰጠው ፈተና 12ኛ ክፍል ለማጠናቀቅ ወይም ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚለውን የሚመልስ ባለመሆኑ በቀጣይ መፈተሽና መስተካከል ይኖርበታልም ተብሏል።
በመጨረሻም ማጠቃለያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ሁሉንም ተማሪዎች በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ ማስተማርና መፈተን እንደማይገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህንን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከፍተኛ ችሎታ፣ ብቃት፣ እውቀትና ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች የምናወጣበት ተቋም ሊኖረን ይገባል በማለት ለዚህም እየተሰራ መሆኑን አንስተው ከታች ጀምሮ ታለንትድ የሆኑ ተማሪዎች የሚወጡበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
በመድረኩ በተሳታፊዎች የተነሱ ሀሳቦች ተይዘው ደረጃ በደረጃ በትምህርት ስርዓቱ ተግባራዊ የሚደረጉ መሆኑን ሚኒስትሩ ማብራሪያ ስጥተዋል።
.

Copyright © All rights reserved.