Notice የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ርዕሳነ መምህራን ለሁለት ቀን የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ርዕሳነ መምህራን ለሁለት ቀን የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

02nd October, 2023

(አዲስ አበባ 18/1/2016 ዓ.ም)  በስልጠናው በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 227 የመንግስት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ስልጠናውም ቀደም ብሎ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተደረገ ድጋፍና ክትትል ሪፖርትን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቀዳማይ ልጅነት ስልጠና ባለሙያ ወይዘሮ ፍሬህይወት በቀለ አስታውቀዋል።ባለሙያዋ አክለውም ላለፉት ሁለት አመታት በከተማ አስተዳደሩ ከቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም አተገባበር ጋር በተገናኘ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የተዘጋጀው ጫወታን መሰረት ያደረገ የማስተማር ስነ ዘዴ በአግባቡ እንዲተገበር ኃላፊነታቸው ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ቀደም ሲል አዲሱን ስርአተ ትምህርት መሰረት አድርጎ በተዘጋጀው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ይዘት ዙሪያ ለመምህራኑ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ባለሙያዋ ጠቁመው ርዕሳነ መምህራኑም በስልጠናው የሚያገኙትን ግንዛቤ መሰረት በማድረግ ለመምህራኑ በቂ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ ሱፐርዛይዘሮችና ርዕሳነ መምህራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸው ቢሮው ትምህርቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

.

Copyright © All rights reserved.