አዲስ አበባ ነሀሴ 23 /2015 ዓ.ም በፊርማ ስነ-ስርዓቱ በኢትዮጵያ የዩናይትድ አረብ ኢምሬት አምባሳደር ሀላል ሀላዚዝ ፣ በኢትዮጵያ የአረብ ሊግ ተወካይ አምባሳደር ዋሊድ ፣ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አመራሮች የአልመክቱል ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ብራንች ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የፊርማ ስነ-ስርዓቱ በዋናነት ለቀጣይ አምስት አመታት በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የተካሄደ ነው።
የአልመክቱም ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ብራንች ዳይሬክተር ሚስተር አብዱሰላም አደም በስምምነት ፊርማ መርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ፋውንዴሽኑ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመፈራረም ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸው ፕሮጀክቱ መቶ ፐርሰንት ውጤታማ እንዲሆን የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ መንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮጵያ የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ኢምባሲ ምስጋና አቅርበዋል።
ሚስተር አብዱሰላም አክለውም ከሴፕቴምበር 1 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው የዛሬው ስምምነት መሰረት በከፍተኛ በጀት በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በሚሰጠው የትኩረት መስኮች መሰረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው አልመክቱም ፋውንዴሽኑ ላለፉት አምስት አመታት ከዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ መንግስት ባገኘው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ተደራሽነትም ሆነ ጥራት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ጠቁመው ይህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ላቅ ወዳለ ደረጃ ያሸጋገረ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።
ዶክተር ዘላለም አክለውም በዛሬው እለት የተፈረመው የስምምነት ፊርማ በፋውንዴሽኑ በሚደገፉ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል ተግባር እንደመሆኑ ቢሮው ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸው አዲሱን ስርአተ ትምህርት መሰረት አድርጎ በ2ኛ ደረጃ የሚሰጠው የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል በአዲስ አበባ ከሚገኘው የሀገሪቱ ኢምባሲ በርካታ ድጋፎች እንደሚጠበቁም አስታውቀዋል።